ኩዊንስ ሱፐርማርኬት የምሥረታ ባንዲራ ቀንን አከበረ
ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም.
ኩዊንስ ሱፐርማርኬት ኃላ.የተ.የግ.ማ. በኩባንያ ደረጃ ተቋቁሞ ወደ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች የተቀላቀለበትን የባንዲራ ቀን ጥር 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ላምበረት በሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት አከበረ፡፡
በቴክኖሎጂ ግሩፑ የሥራ ባህል መሠረት አዲስ ኩባንያ ሲቋቋምና ወደ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች በአባልነት ሲቀላቀል የባንዲራ ቀን የማክበር ልምድ በመኖሩ በኩዊንስ ሱፐርማርኬት የተዘጋጀው በዓልም ይህንኑ የሚያመለክት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሠር ዶ/ር አረጋ ይርዳውን በመወከል በበዓሉ መክፈቻ ወቅት በእንግድነት የተገኙት የሚድሮክ ሲኦኦ ፕሪንሲፓል ኦፕሬሽን ኦፊሠር ሰብ ግሩፕ ኤ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሀጐስ ኩዊንስ ሱፐርማርኬት አሁን ለደረሰበት የጥሩ አገልግሎት አሠጣጥና የማስፋፋት ሥራ ሁሉም ሠራተኞች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
አቶ ጌታቸው ኩባንያው በቀጣይ ዘመናዊ አደረጃጀትና አሠራርን በመከተል በአገልግሎት አሠጣጡ በአንደኛ ደረጃ ተመራጭ የሚሆንበትን ሥልት በመከተል ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገር እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ኤፍሬም ታደለ በበኩላቸው ኩባንያው አሁን ለደረሰበት የዕድገት ደረጃ በሁሉም አመራር አካላት የተደረገለትን ከፍተኛ ድጋፍ አመስግነው፤ ለወደፊቱ ለተጠቃሚዎች ዕርካታ ሁሉም ሠራተኛ አስፈላጊ የሆነውን ተግባር በማከናወን በትጋት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡
ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ስድስት ቅርንጫፎች ሲኖሩት በቀጣይም ቅርንጫፎቹን የማስፋት ዕቅድ ያለው ሲሆን፤ በዋናነት የኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላ.የተ.የግ.ማ. ምርቶችን እንዲሁም ሌሎች የመገልገያ ቁሶችን ለሽያጭ በማቅረብ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
በበዓሉ ላይ የኩባንያው ሠራተኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን፤ የኩባንያውንና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ባንዲራ የመስቀል ተግባር ተከናውኗል፡፡