14ኛው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች እና ተጋባዥ ተቋማት ዓመታዊ የስፖርት ውድድር ፍጻሜ በሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታዲየም እንደሚደረግ ተገለጸ
የካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም
* ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የ3 ሚሊየን ብር ቦንድ ለመግዛት ቃል ተገባ
![]() |
ዶ/ር አረጋ ይርዳው በበዓሉ መክፈቻ ላይ ንግግር ሲያደርጉ |
በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አዘጋጅነት ለ14ኛ ጊዜ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ኩባንያዎችና ተጋባዥ ተቋማት መካከል የሚካሄደው ዓመታዊ የስፖርት ውድድር የካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም በመቻሬ ሜዳ ኮርፖሬት ሴንተር ግቢ በድምቀት ተጀምሯል፡፡
የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ዶ/ር አረጋ ይርዳው በዚህ ዓመታዊ የስፖርት ውድድር መክፈቻ በዓል ላይ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር፤ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀመንበርና ባለሀብት ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በባለቤትነት የሚመሩዋቸውን ኩባንያዎች ሠራተኞች የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጎልበት፣ ጤናማ የኩባንያ የሥራ ሰላም ለማስፈን፣ አዳዲስ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማበረታታት እና በኩባንያዎቹ መካከል የወዳጅነት መንፈስን ለማጠናከር በየዓመቱ በሚድሮክ ሲኢኦ (CEO) ቴክኖሎጂ ግሩፕ አዘጋጅነት በሚካሄደው በዚህ ደማቅ የስፖርት ወድድር መክፈቻ በዓል ላይ በመገኘታቸሁ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ ብለዋል፡፡
ዶ/ር አረጋ ይርዳው በዚሁ ንግግራቸው፣ የሚድሮክ ቴከኖሎጂ ግሩፕ 25 ኩባንያዎችን በአራት የቴክ ምድብ በመመደብ እንዲሁም 11 ሌሎች ተጋባዥ እህት ኩባንያዎች እና ተቋማት በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ለመወዳደር ዝግጅታችሁን በማጠናቀቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም በቀጣይ ወራቶች እንደወትሮው ሁሉ በድምቀትና በመልካም ሥነ-ምግባር የሚካሄደውን የ2009 ዓ.ም 14ኛውን የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች እና ተጋባዥ ተቋማት ዓመታዊ የስፖርት ውድድር ዛሬ በይፋ መከፈቱን ስገልጽ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል፡፡
ዛሬ የዓለም አቀፍ ሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ሩጫ በከተማችን እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንደተለመደው በቦታው ባለመገኘታችን ያሳደረብኝ ሰሜት ቢኖርም ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ሩጫ በዓል ጋር የስፖርት በዓላቸውን በሚያከብሩት 25 የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ሥም 3ሚሊየን ብር ቦንድ በመግዛት ምን ጊዜም የልማት አጋር መሆናችንን እገልጻለሁ፡፡
በተለይ ሴቶች እናቶች፣ ሚስቶች፣ እህቶች፣ ልጆች አና አጋሮች ሆነው የተፈጠሩ በመሆናቸው ልዩ አክብሮት ሊቸራቸው ይገባል ያሉት ዶ/ር አረጋ በመጪው ረቡዕ የካቲት 29 ቀን 2009 ዓ.ም የሴቶችን ቀን በማስመልከት በመቻሬ ኮርፖሬት ሴንተር ልዩ ዝግጅት እንደሚደረግ ከወዲሁ ለመግለጽ እወዳለሁ ብለዋል፡፡
በዚህ አጋጣሚ በየዓመቱ በውጪዎቹ የሚከበረውን የእናቶች ቀን ከውጭዎቹ ባሻገር በሀገራችን ባህል መሠረት በኩባንያዎቻችን እንዲከበር ለማድረግ ከውዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋችንን እገልጻለሁ ያሉት ዶ/ር አረጋ ይኼው የ2009 ዓ.ም የእናቶች ቀን በዓል በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ሠራተኞች እንዲከበርና በሠራተኞቻችን መካከል ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ለትውልድም እንዲተላለፍ ለማድረግ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረከታለን፤ በተለይም አምና ይህንኑ የእናቶች ቀን በማዘጋጀት ረገድ አርአያ የሆኑትን ላመሰግን እወዳለሁ ብለዋል፡፡
ዶ/ር አረጋ ይርዳው በዚሁ ንግግራቸው ሊቀመንበራችን ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በባለቤትነት ከሚመሩዋቸው ከ70 በላይ ኩባንያዎች መካከል የሚድሮክ ቴከኖሎጂ ግሩፕ 25 ኩባንያዎችን እና 11 ተጋባዥ እህት ኩባንያዎች እና ተቋማት ብቻ በዓመታዊ ሰፖርት ውድድሩ ላይ ተሳታፊ መሆናችሁ በቂ ባለመሆኑ የሚድሮክ ቴከኖሎጂ ግሩፕ በፈጠረው ምቹ የስፖርት ሁኔታ በመጠቀም የሁሉም ኩባንያዎች ተወዳዳሪ ስፖርተኞች ተሳታፊ እንዲሆኑ ይበረታታሉ ብለዋል፡፡
በመጪው ዓመትም በ15ኛው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች እና ተጋባዥ ተቋማት ዓመታዊ የስፖርት ውድድር የየኩባንያዎቹ የሠራተኞች ልጆች የእግር ኳስ ቡድን ተቋቁሞ ዓመታዊ በዓሉን እንዲቀላቀል ለማድረግ ወስነናል ብለዋል፡፡
በየዓመቱ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አዘጋጅነት የሚካሄደውን ዓመታዊ ሰፖርት ውድድር የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው የመዝጊያው ሥነ-ሥርዓት የሚካሔደው በሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታዲየም እና የወጣቶች ማዕከል መሆኑን ያበሰሩት ዶ/ር አረጋ ይርዳው ለዚሁ ቅድመ ዝግጅት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በስፖርት ውድድሩ መክፈቻ ዕለት ከሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አራት ምድቦች መካከል የቴክ መገናኛ እና የቴክ አቃቂ የእግር ኳስ ቡድኖች በዙር ውድድር ተጋጥመው የቴክ መገናኛ ቡድን የቴክ አቃቂ የእግር ኳስ ቡድንን 3ለ2 ረትቷል ፡፡
ዛሬ የተጀመረው ይኼው ዓመታዊ የስፖርት ውድድር፣ እግር ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ገመድ ጉተታ፣ ሜዳ ቴኒስ፣ ሩጫ፣ ዱላ ቅብብል፣ ቼዝ፣ ዳማና ሌሎችም ልዩ ልዩ የስፖርት ዓይነቶች የሚካሄዱበት እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሲኢኦ (CEO) ቢሮ አዘጋጅነት በሚካሄደው ዓመታዊው የወዳጅነት የስፖርት ውድድር የቴክኖሎጂ ግሩፑ ኩባንያዎች የሆኑት፤ ቴክ ሣር ቤት፣ ቴክ አቃቂ፣ ቴክ መገናኛ፣ ቴክ ሰሚት እንዲሁም አስራ አንድ ተጋባዥ ኩባንያዎች እና ተቋማት ማለትም፤ ፖልሪያስ፣ ዳሸን ባንክ፣ ኢትዮ ቴሌኮም (ደቡብ ምዕራብ ቀጠና ቅርንጫፍ)፣ ናሽናል ሞተርስ፣ ሞሐ ለስላሳ መጠጥ ኢንዱስትሪ (የንፋስ ስልክ ፋብሪካ)፣ አዲስ ኢንተርናሽናል ኬተሪንግ፣ ኒያላ ኢንሹራንስ፣ ሆራይዘን አዲስ ጎማ፣ ኢኳቶሪያል ቢዝነስ ግሩፕ፣ ኢትዮ ሌዘር ኢንዱስትሪ እና ሜፖ ኮንስትራክቲንግ እና ማኔጅመንት ሰርቪስ ተካፋይ ይሆናሉ፡፡
በስፖርት በዓሉ መክፈቻ ላይ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ከፍተኛ የሥራ አመራር አባላት፣ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው፣ የተጋባዥ ኩባንያዎች እና ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
![]() |
የየኩባንያዎቹ ተወዳዳሪዎች በክብር ትሪቢዩን ፊት ሲያልፉ |