የቴክኖሎጂ ግሩፑ ኩባንያዎች የሠራተኛ ማኅበራት የህብረት ስምምነት ፊርማ ተፈራረሙ
ጥር 9 ቀን 2006 ዓ.ም.
የኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላ.የተ.የግ.ማ፣ የሰሚት ኢንጂኔርድ ፕላስቲክ ኃላ.የተ.የግ.ማ እና የብሉ ናይል የፖሊፕሮፕሊንና ክራፍት ከረጢት ማምረቻ ኃላ.የተ.የግ.ማ. የአመራር አባላትና የሠራተኛ ማኅበራት ጥር 8 ቀን 2006 ዓ.ም. በግሎባል ሆቴል ለ3ኛ ጊዜ የህብረት ስምምነት ፊርማ ተፈራርመዋል፡፡
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሠር ዶ/ር አረጋ ይርዳው አመራሩ ሠራተኛ ተኮር መርህ በተግባር በማዋሉ በየኩባንያዎቹ ያሉ ሠራተኞች ኩባንያውን እንደራሳቸው ንብረት እንዲንከባከቡና ተጠቃሚ አንዲሆኑ ያስቻለ ተግባር እየተፈፀመ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ለኢንዱስትሪ ሠላም፣ ለኩባንያዎቹና ለሠራተኞች ዕድገት መደራጀት አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር አረጋ፤ እስካሁን የተመሠረቱት ስምንቱ ማኅበራት በጋራ በተጨማሪ አንድ ማኅበር እንዲመሠርቱና የመረጃ መለዋወጥ፣ የሀሳብ መደጋገፊያና የመወያያ መድረክ እንዲፈጥሩ አሳስበዋል፡፡ ዶ/ር አረጋ በማንኛውም ኩባንያ ውስጥ የአሠራርና የአመራር ግድፈት ሲያጋጥም በየደረጃው ተወያይቶ መፍትሔ መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ዶ/ር አረጋ አያይዘውም ሠራተኞች በይበልጥ ተግተው የላቀ ውጤት ሲያስመዘግቡና ምርታማ ሲሆኑ የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እድል ይፈጥራሉ፤ ለዚህም ውጤታማነት በርትተው ኩባንያቸውን ማሳደግ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል፡፡
ከየሠራተኛ ማኅበራቶቻቸው ጋር የተፈራረሙት የየኩባንያዎቹ ዋና ሥራ አስኪያጆች በበኩላቸው የቴክኖሎጂ ግሩፑ አመራር ለሠራተኞች በሠጠው ከፍተኛ ትኩረት ሙሉ መብቶችና ጥቅሞቻቸው ተከብረው እንደሚገኙና ወደፊትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያለፈው የአሠራር ልምድ አመላካች መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከየኩባንያዎቻቸው የሠራተኛ ማኅበራት የተወከሉት አመራሮች በበኩላቸው የሠራተኛውን መብትና ጥቅም የሚያስከብረው የሕብረት ስምምነት መፈረሙ ለደምቡ ያህል እንጂ የሲኢኦ አመራር ሠራተኛው ማግኘት ከሚገባው በላይ ጥቅማቸው አንዲከበር ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት የሠራተኛ ማኅበራት ተወካዮች፣ የሲኢኦ ቢሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው አንግዶች ተገኝተዋል፡፡
![]() |
የኤልፎራ የሠራተኛ ማኅበር ተወካይ እና የኤልፎራ ዋና ሥራ አስኪያጅ የህብረት ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅት | ![]() |
የሰሚት የሠራተኛ ማኅበር ተወካይ እና የሰሚት ዋና ሥራ አስኪያጅ የህብረት ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅት | ![]() |
የብሉ ናይል የሠራተኛ ማኅበር ተወካይ እና የብሉ ናይል ዋና ሥራ አስኪያጅ የህብረት ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅት |