12ኛው የኩባንያዎች ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ተካሄደ
ጥቅምት 30 ቀን 2006 ዓ.ም.
![]() |
የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች 12ኛው ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ጉባዔ ጥቅምት 26፣ 27 እና 29 ቀን 2006 ዓ.ም. መቻሬ ሜዳ በሚገኘው የቴክኖሎጂ ግሩፑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄደ፡፡
ስብሰባውን የከፈቱት የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሥራ አፈፃፀም ግምገማ አላማ ያለፈውን ዓመት ዕቅድና የሥራ አፈፃፀም አስተያይቶ ችግሮችን በማረም በጐ ጐኖችን አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችል መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር አረጋ አያይዘውም የዘንድሮው ዓመታዊ የኩባንያዎች የሥራ አፈፃፀም ባለፉት ዓመታት ይሳተፉ ከነበሩት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተጨማሪ በተለየ መልኩ በርካታ የኩባንያዎች የማኔጅመንት አባላትን ማሳተፉ ተተኪ የአመራር አካላት ልምድ እንዲያገኙ የታቀደ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በስብሰባው የእያንዳንዱ ኩባንያዎች የግብይትና ሽያጭ ሥርዓት፣ የሂሳብ አያያዝና አጠቃቀማቸው፣ የሰው ኃይል ስምሪት፣ በቀጣይ ያቀዷቸው የማጠናከሪያና የማስፋፊያ ሥራዎች በዝርዝር በየኩባንያዎቹ ዋና ሥራ አስኪያጆች አማካይነት ቀርበው የተፈተሹ ሲሆን፤ ከተሰብሳቢዎች ለሚነሱ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
በስብሰባው ማጠቃለያ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ባለፈው ዓመት ኩባንያዎቹ ባስመዘገቡት የሥራ አፈፃፀምና ባስገኙት የገቢ መጠን ልክ ተሰልቶ ዓመታዊ የሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ እንደሚደረግ ይህም ሣይንሳዊ የአሠራር ሥርዓትን ተከትሎ የሚፈፀም መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ዶ/ር አረጋ የኩባንያዎቹ የአመራር አካላት ከሠራተኞች ጋር በጥምረት በተያዘው የበጀት ዓመት ጠንክረው በመሥራት የተሻለ የሥራ አፈፃፀም ውጤት እንዲያስመዘግቡና ለእድገት አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ በከፍተኛ ትጋት መነሳት አንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡
በዚህ ስብሰባ ከሃያዎቹ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች የተውጣጡ ከ150 በላይ ተሳታፊዎች ተካፋይ ሆነዋል፡፡